ብዙዎቻችን ምንም ምን ሊገባን ያልቻለው ጉዳይ ይህ ነው፡፡ ይህ አደገኛና አጥፊ ርኩስ ጠላት የተጣለው የት ነው? የት ነው አሁን የሚገኘው ? የሚለውን አንመልስም፡፡ ደግመን ልብ እንበል" የወንድሞቻችን ከሳሽ ወደ #ምድር ተጥሎአልና"
ይሄ ከሳሽ የተጣለው ወደ ምድር ነው፡፡ ወደ ሰማይ አይልም፡፡ እኛ የምንኖርባት ፣ ጎጆ የምንቀልስባት ፣ የምንሠራባት ፣ የምንማርባት ፣ ቤተሰብ የምንመሠርትባት ፣ ከፍሬዋም ከምንመገብላት ምድራችን ላይ ነው የተጣለው፡፡ ስለዚህ በምድር ተቀናቃኝ አለብን ማለት ነው፡፡ ባለጋራ አለብን ማለት ነው፡፡ አኗኗሪ አለብን ማለት ነው፡፡ ይህንን በጣም ማስተዋል አለብን፡፡
የኛና የዲያብሎስ ውጊያ የሚያቆመው የተጣለባትን ምድር ለቀን ስንሄድ ነው፡፡ ያኔ ወይ ከእግዚአብሔር መንግሥት ተገኝተን የክብሩ ወራሾች እንሆናለን፤ ወይ ከጨላማው ቦታ ተገኝተን ከተጣለው ርኩስ ጋራ አብረን የጨለማን ፍርድ እንቀበላለን፡፡ ሌላ 3ተኛ አማራጭ የለም፡፡ ወይንም ገለልተኛ የምንሆንበት የአኗኗር ዘይቤ የለም፡፡ ፈለግነውም አልፈለግነውም ወይ ከብርሃኑ አሊያ ከጨለማው ነን፡፡
ሰይጣን ለምንድነው ታዲያ እንዲህ አጥብቆ የሚፈትነን ? ምድርን ለቀን እስክንሄድ ለምን ይታገለናል ? የሚል ጥያቄ እናነሳ ይሆናል፡፡ ለዚህ ብዙ በሃይማኖታዊ ታሪክ ውስጥ ካሉ እውነታዎች በመነሳት አስተንትኖቶችና ማብራሪያዎች መስጠት ይቻላል፡፡ ከነዚያ መካከል አንዱን ለመመልከት እንደዚህ የሚለውን ቃል ስናጤን የምናገኘው ጉዳይ ነው፡፡
"በሰማይም ሰልፍ ሆነ፣ ሚካኤልና መልዐክቱ ዘንዶውን ተዋጉ፡፡ ዘንዶውም ከእነርሱ ጋር ተዋጋ፣ አልቻላቸውም፣ ከዚያም ወዲህ #በሰማይ ስፍራ #አልተገኘላቸውም"ራእይ 12፥7-12
በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውሞ አለ፡፡ ዲያቢሎስ ወደ ሰማይ የሚመለስበት መንገድ ቆሟል፡፡ ዳግም ከሰማያውያን ጋራ ሊቀላቀል አይችልም፡፡ ስፍራ አልተገኘላቸውም ነው፡፡ ከወደ ሰማዩ ቦታ የለውም በቃ፡፡ ስለዚህ የተጣለባት ምድር ርስቱ ነች፡፡ የማቴዎስ ወንጌል ምዕራፍ 4፥8'ን አስተውሉ፡፡
"ደግሞ ዲያቢሎስ እጅግ ረጅም ወደ ሆነ ተራራ ወሰደው፥ #የዓለምንም_መንግሥታት_ሁሉ_ክብራቸውንም_አሳይቶ። ወድቀህ ብትሰግድልኝ ይህን ሁሉ #እሰጥሃለሁ አለው። ያን ጊዜ ኢየሱስ። ሂድ፥ አንተ #ሰይጣን ለጌታህ ለአምላክህ #ስገድ እርሱንም ብቻ #አምልክ ተብሎ ተጽፎአልና አለው።
የዓለምንም መንግሥታት ሁሉ ክብራቸውንም አሳይቶ ይላል፡፡ የሚገርም ነው፡፡ ዓለምን ለፈጠረው ጌታ የዓለምን መንግሥታት አሳየው፡፡ ሁሉን ኃይል ለያዘ ንጉሥ የዓለምን ኃይል አሳየው፡፡ ተመልከቱ ጌታችን እዚህ ጋር ሁለት ነገሮችን አስተምሮናል
አንደኛ ☞ ሂድ አንተ ሰይጣን ለአምላክህ ስገድ እርሱንም ብቻ አምልክ ተብሎአልና ሲለው የዲያቢሎስን ክንድ መስበሪያ በአምልኮት መመላለስና ስግደት እንደሆነ ሲያስተምረን ነው ፡፡ መንበርከክ ስትጀምር አጋንንትን ታንበረክካቸዋለህ፡፡ ከፍቅር ጀምረህ የራእይ አምልኮትን መስጠት ስትጀምር ክፉውን ሂድ ትለዋለህ፡፡ በመስገድ ኃይል ውስጥ የእግዚአብሔርን ክብር ስለምትገልጥ ጠላትህ ሊቋቋምህ አይችልም፡፡
ሁለተኛ ☞ የዓለም መንግሥታትን ክብራቸውን ሁሉ አሳየውና ይላል፡፡
ለዚህ ነው ምድር ርስቱ ነች የሚባለው፡፡ የምድራዊ ብቻ ክብር መግለጫ ዲያቢሎስ ነው፡፡ የዓለምን መንግሥታት ነው፡፡ የዲያቢሎስ አሠራርና ስልት አንዱ ትላልቁን ቀድሞ የመያዙ አካሄድ ነው፡፡ የዓለምን መንግሥታት እንደሚቆጣጠር አሳየውና ስገድልኝ አለው፡፡ ሰይጣን ብዙ ጊዜ በትላልቅ ቦታዎችና የክብር መገለጫዎች ራሱን ለመግለጥ ይቸኩላል፡፡ ደሞ እነዚህን ሁሉ እሰጥሃለሁ ነው ያለው፡፡ በባለቤትነት የተቆጣጠረው የምድሩን መንግሥታት ነውና ሁሉንም ልስጥህ አንተ ብቻ ወድቀህ ስገድልኝ አለ፡፡
ይህንን እሰጥሃለሁ ያለውን ቃል ስናስተውል ምድር ርስቱ እንደሆነች በሚገባ እንገዘባለን፡፡ የዓለም ገዢ ሲባልም ምን ያህል በምድር በኩል ያገኘውን የክፋት ኃይልና በሰው ልጆች ሕይወት ውስጥ የሚከፍተውን የማያባራ ጦርነት ለማሳሰብ ነው፡፡
እኛ ግን በሰማይ ስፍራ ይገኝልን ዘንድ በዳግማዊ አዳም በጌታችን በመድሃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የእግዚአብሔር ልጅነትን አግኝተናል፡፡ ቃሉ እንደዚህ ይለናል፡፡
"ዮሐ .1፥12 : ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው"
የእግዚአብሔር ልጅነትን ሥልጣን መቀበል ለሰው ልጆች ሁላችን የተሰጠ የመለኮት ስጦታችን ነው፡፡ ይህንን የጸጋ ኃይል እኛ ሳናውቀው ወይንም ሳንረዳው ዲያቢሎሱ አውቆት ይህንን ሥልጣን ሊነጥቀን እረፍት ሳያደርግ ይታገለናል፡፡ በጌታችን የሥጋ መገለጥ ሚስጥር ውስጥ አምላክ ሰው፤ ሰው አምላክ የሆነበት ጥበብ ለሰው ልጆች የተሰጠ የቃልኪዳኑና የሰማያዊ ቃሉ ኃይል ነው፡፡ ሰይጣን ይህንን ስለሚያውቅ የአምላክነት ጸጋውን እንዳትካፈል በጉዞህ መካከል ይቆማል፡
በኛም ሕይወት ውስጥ ክፉው መንፈስ ይህንንን መረጃ ለመጠቀም ሲጀምር በመጀመሪያ ልብህን ያጠናል፡፡ ሰማያዊ ጸጋህን ከልብህ ውስጥ ካለው ቦታ ጋር እያነጻጸረ በደንብ ያጠናሃል፡፡ አንሸወድ በእውነት፡፡ ዲያቢሎስ ያለመረጃ ስንዝር አይንቀሳቀስም፡፡ መውጫ መግቢያህን ሳያጠና አይይዝህም፡፡ አኗኗርህን ሳይገነዘብ ሥራውን አይጀምርም፡፡ ከውስጥህም ገብቶ ደሞ ስላንተ ያለውን መረጃ ማጥናቱን ይቀጥላል፡፡ ይዞታውን የሚጀምረው ከውስጥህ ካለው መረጃ በመንተራስ ነው፡፡ ልማድህን እስኪለምደው ቦታና ጊዜ ሰጥቶ በእቅዱ አካሄድ እየገመገመህ ቁጭ ብሎ ይቃኝሃል፡፡
በጣም መንቃት አለባችሁ፡፡ ትልቁ ጦርነታችን ሰማያዊ ርስታችንን ከመረከብና ከመነጠቅ መካከል ባለው የሰይጣን ትግል ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ እናንተም መረጃ ያዙ፡፡ በአምልኮት በኩል ያለው መረጃ ደሞ የሚመጣው በመንበርከክ ውስጥ ነው፡፡ ሰብአ ሰገል በህልም ወደ ክፉው እንዳይመለሱ መረጃ ያገኙት ወድቀው ከሰገዱ በኃላ ነው፡፡